Author Archives: admin

አፈወርቅ ተክሌ

እንደ ተከበሩ ሰዓሊ ወንድማችን ያለ ተልእኮውን ፈጽሞ ላለፈ ባለሙያ፡ ፈጣሪ ያዘጋጀለትን ሩጫ ጨርሶ ከሚወደው ወገኑ በሞት ሲለይ፡ ስለተደነቀበት ችሎታው ወዳጅ ዘመድ ብቻ ሳይሆን ጠላትም እጅግ ጎልቶ በመታየት ላይ ያለውን ተግባር፡ ከመሰወር ይልቅ ራሱን በሚጠቅመው መንገድ ይናገረዋልና የነ አባ ጳውሎስ በሰዓሊ አፈወርቅ አሸኛኘት ስርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር ካብ አይገባ ድንጋይ ነው። አጥምቃና የተደነቁበትን የሙያቸውን መሰረት አስጨብጣ፡ እማማ ኢትዮጵያ የሚለውንም መንፈስ በስሜታቸው ቀርጻ ሰዓሊ አፈወርቅን ወደውጭ ስለላካቻ ቸው ቤተ ክርስቲያናችን ባጭሩ ተናግሬ ወደ አዘጋጀኋት አማረኛ ቅኔ እሻገራለሁ

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

እግዚአብሔር የቀባው

አባ ማትያስ ተመረጥኩ የሚሉበት ወቅትና አፈጻጸሙ በቤተ ክርስቲያናችን መመሪያ ሲለኩ የእምነት፥ የእውቀትና የሞራል ጉድለት ያለባቸውንና የማያውቃቸውን አባ ማትያስን የመሰለ ሰው የኢትዮጵያ ህዝበ ክርስቲያን ሊመርጥ ይቅርና ብቃት ያለው እንከን የማይገኝለት ሰው እንኳ በዚህ ወቅት አይመርጥም። ይህንን የመሰለ አጥፊ መንግስት ጥፋቱን የሚፈጽመበት መሳሪያ የሚሆን ሰው ለማግኘት ያለውን ሁሉ ኃይል በመጠቀም ለማጭበርበሪያ ምርጫ ከ፭፻ ሰውም በላይ መሰብሰብ ይችላል:: ይህን የተረዳ ብቃት ያለው ሰው ይሸሻል እንጅ፤ አባ ማትያስን የመሰለ የጥፋት ተባባሪ ካልሆነ በቀር አይገባበትም። የተጀመረው እርቅ ሳይፈጸም ምርጫ እንዳይታሰብ እያለ ህዝቡ የሚያስተጋባውን ድምጽ ደምስሶ ተመረጥኩ ካለ፤ መመሪያችን ምቱር ነህ ይለዋል እንጅ ቅዱስ ብጹዕ ፓትርያርክ ነህ በማለት አይቀበለውም። አባ ማትያስ በዚህ አይነት ግርግር ወደ መንበረ ፓትርያርኩ እንደመጡ እራሳቸው እያወቁ
ሳያስቡትና ሳያልሙት ድንገት በተአምር እንደወደቀባቸው ለማስመሰል “በፈቃደ እግዚአብሄር ተመረጥኩ” ማለታቸው የእግዚአብሄርን ስም በከንቱ የሚጠቀሙ “ቢጽ ሀሳዊ” (ወገን መስሎ የገባ አታላይ ዋሾ) ነው በማለት መልስ ልንሰጣቸው የሚገባን እንጅ “እግዚአብሄር የቀባህ” ብለን መቀበል የውሸቱ ተካፋይ መሆን ነው።
ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

ከካንሳስ ደብረ ሣህል መድኃኔ ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ስለ አቡነ ሽኖዳ ፫ኛ ሐዋርያዊ ተልእኮ ጠንካራ አቋም፡ የተሰጠ ታሪካዊ ምስክርነት

ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ሽኖዳ “በኃይል ጩህ አትቆጠብ ድምጽህንም እንደ መለከት አሰማ”(ኢሳ ፶፰፡፩) ተብሎ ለነቢዩ ኢሳይያስ የተሰጠውን መለኮታዊ ትእዛዝ እና፤ ቅዱስ ጳውሎስም “በጊዜውም ያለ ጊዜውም ጽና ፈጽመህ እየታገስክና እያስተማርክ ዝለፍና ገስጽ ምክረም።ህይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሱበት ዘመን ይመጣል”(፪ ኛ ጢ ፬፡፪) ብሎ ለጢሞቴዎስ በአጽንኦ የተናገረውን ሐዋርያዊ ግዴታ ለህዝባቸውና ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት በመጮህ ተወጥተው፤ ዘመናቸውን በመዋጀት ያለፉ የተባረኩ አባት ነበሩ።

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

“የካህናት ዜና ዕረፍት ሚዛን” የመምሬ አሰፋ መኮንን የሕይወት ታሪክ

ከግብአተ መሬት በኋላ በመቃብር ላይ መነበብ ያለበት ዜናሕይወት ለፖለቲካ መሪ በዘመኑ የፈጸማቸው ክፉና ደግ ሥራዎቹ፤ ዳኛ ከሆነ በሚዛናዊ ፍርዱ፤ ወታደር ከሆነ አገር ለመታደግ የፈጸመው ጀብዱ፡ አራሽ ገበሬ ከሆነም መልካም ግብርናው፤ የቤት እመቤት ከሆነች ባልትናዋ፡ እናትነቷ፡ ጥበቧና የህይወት ምንጭነቷ፡ በማነኛውም አገልግሎት ተሰማርተው በመልካም የፈጸሙ ሁሉ፡ የፈጸሙት መልካም ተግባር እየተዘረዘረ ከነ እገሌ ከዚህ መንደር ተወለዱ እየተባለ ይነበብላቸዋል። የካህናት ዜናእረፍት ግን በስሜ አጥምቁ ባለው መሰረት ያጠመቁትን ሁሉ ስሙን ከክርስቶስ ጋራ በማወራረስ፡ ዘሩን በሱ በኩል እንዲቆጥር በማስተማር ሲፈጽሙ የኖሩትን ተልእኮ የሚያንጸባርቅ: ፍጥረትን በየወገኑና በየዘመዱ በፈጠረው በእግዚአብሄር ግብርና በቆሙባት በኦርቶዶክሳዊት ነገረ መለኮትና አስተምህሮ ላይ መመስረት አለበት።

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

ኃያላን ይጽሕፉ ጽድቀ

ባለፈው ጥቅምት ወር ፳፻፬ ዓ.ም. ቅዱስ እያለ ራሱን ከሚጠራበት ቅጽል ጋራ በመላተም ከሰነበተው ሲኖዶስ ባቢሎናዊ ዝብርቅርቅ እየመነጨ በድኅረ ገጾች ወደ ህዝበ ክርስቲያኑ ሲጎርፍ ሰንብቷል። ቅድስና ሊቀጸልለት የሚገባው; እንደ ሐዋርያት ሲኖዶስ “እስመ ኀብረ መንፈስ ቅዱስ ምስሌነ” (የሐዋ፲፭፡፳፱) በማለት፦ የሰላም የመረጋጋትና የማስተዋል ምንጭ መንፈስ ቅዱስ መሪያችን ነው ብሎ በቃሉ መስክሮ በግብሩ አረጋግጦ ያመረተውን ሰላም መረጋጋትና ማስተዋል ምእመናን ሲያፍሱት ብቻ ነበር። ይሁን እንጅ በአቡነ ጳውሎስ ከሚመራው ሲኖዶስ ሲመነጭ የሰነበተው በሜዳ ከሚጫወቱ ሕጻናት የማይጠበቅ ሁካታ ይመስል እንደነበር ሲከታተል የነበረ ሰው ሁሉ ሲነጋገርበት ሰንብቷል። ይህ የሜዳ ጨዋታ አይነት ሁካታ በዚህች ቤተ ክርስቲያን የተሰየመውን ካህን ይቅርና፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጭ የሆነውንም እንኳ ምን አይነት ሲኖዶስ ነው? ብሎ እንዲጠይቅ የሚያደርግ ነው።
ይልቁንም የቤተክርስቲያኒቱ አካል ነኝ ለሚል በግሌ ምን ማድረግ ይገባኛል? ብሎ ራሱን እንዲጠይቅ የሚገፋፋና የሚያስገድድድ ይመስለኛል።

እንዲያውም ክርስቶስ ምሳሌ አልባነቱን በምሬት የገለጸው አይነት ስብሰባ ይመስላል። ክርስቶስ የዮሐንስን ደቀ መዛሙርት አነጋግሮ ከሸኘ በኋላ ሰዎች ከእምነቱና ከወቅታዊው ችግር ጋራ የማይገናኝ ነገር ሲነጋገሩ ሰማና “ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆ ወይስ ቀጭን ልብስ የለበሰው ሰው ለማየት ነው የመጣችሁ?” እያለ አቋም የለሽነታቸውንና አላማ ቢስነታቸውን ነገራቸው። ቀጠለና “የዘፈን ዜማ አቀነቀንላችሁ አልተቀበላችሁም፡ የልቅሶ ዜማ አቀነቀንላችሁ አልተቀበላችሁም፡ ይህን ትውልድ በምን ምሳሌና እንዴትስ ልግለጸው” (ማቴ ፲፩፡፲፮_፲፰) እያለ ለአላማና አቋመ ብልሹነታቸው አቻና ወደር የሌላቸው መሆኑን በምሬት ተናገረ።

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

“ክፉ ዘመን” ዘመነመንሱት (ፈታኝ ዘመን)

ስለ ኢትዮጵያና ስለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አዲስ መጽሐፍ ተደርሶ ወጣ ሲባል አግኝቼ ለማንበብ በጣም እናፍቃለሁ። ሲደርሰኝ “እግዚኦ ተሣሃላ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ አግርር ላቲ ጸራ …… ወስካ አሚነ ወሃይማኖተ ተናገር ውስቴታ በእንተ አብያተ ክርስቲያናቲከ ሀባ ሰላመ፡ በእንተ ኩሉ ህዝብከ ከመ ንህነኒ ዕሩፈ ነሀሉ በሰላም” (ዘይነግሥ) በሚለው መጽሐፈ ጸሎታችን እመዝነዋለሁ። ይህም ማለት “አቤቱ ስለ ህዝብህ ስትል አገራችንን ኢትዮጵያን ማራት ከእምነት መናወጽ ጠብቀህ በአንድነቷ አቆያት። ሁላችንም በተረጋጋ ህሊና እረፍትና በሰላም እንኖርባት ዘንድ በውስጧ ባሉት አብያተ ክርስቲያናት ጽድቅህንና ሰላምህን አስፍን”።

በነሐሴ ወር The Wisdom Compass to Eternal Life የተባለውን መጽሐፍ ደራሲው ልኮልኝ ካነበብኩት በኋላ ከአገር እና ከቤተ ክርስቲያን ጋራ ምን ዝምድና አለው? ለዚህ ትውልድስ ምን መልእክት አለው? ለራሴስ ምን ያስተምረኛል ብዬ መጽሐፉን ከላይ በገለጽኩት መለኪያ ለካሁት፤ መዘንኩት። ስኑትዩ የተባለው ኦርቶዶክሳዊው ሊቅ “ወንህነሰ ንትዌከፍ ትምህርታቴሆሙ ዘመሀሩን ወነአምን ቃላቲሆሙ ዘተፈነወ ለነ እምኔሆሙ እሁዛን በትምህርትነ ዘተምሀርነ ወጽኑአን ንህነ እንበለ ተወላውሎ”( ስኑትዩ ፻፲፡፲፬) እንዳለው። ካነበብኳቸው ብዙዎቹ ይህ መጽሐፍ የአገራችንን ቀዳማዊና አሁን ያለችበትን ሁኔታ የዳሰሰ ከቤተ ክርስቲያናችን ስርአተ አምልኮት ሳይወጣ በመሠረታውያን ቅዱሳት መጻህፍት አጀማመር ተጀምሮ: በአፈጻጸማቸው የተፈጸመ ግእዙን ከዘመኑ ቋንቋ ይህን ትውልድ ከቀደመው ትውልድ ጋራ አነጋጋሪ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

ደመራ : በሃይማኖታችን፥ በታሪካችንና በባሕላችን አንጻር

‘ደመራ’ ደመረ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተወሰደ ነው:: ትርጉሙ ጭመራ ማለት እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው:: ጥሪት (ካፒታል) እንዳይጎድል እንዳይቀነስ ይልቁንም እየበዛና እያደገ እንዲቀጥል ጠብቆ መያዝ የሚያስችል ደመራ ነው:: ስሙ እንደሚያመለክተው ማስታወሻነቱ ለተጠራቀመ፥ ለተሰበሰበና ለተጨመረ ነገር ነው:: በያመቱ የምናከብረው የደመራው በዓል በድመር አካቶ የያዛቸዉ ማለትም፦ ሥርዓቱ የሚከናወንባቸው ቁሳቁሶች፥ የሚደመሩት እንጨቶች፥ ችቦዎች፥ አሽክቶችና፥ ሌሎችም የሕዝቡን ስሜት ለመቀስቀስ በወቅቱ የሚዘመሩትና የሚቀሰቀሰውን ህዝባዊ ስሜት አንድ ላይ ሰብስቦ ስለያዘ ደመራ ተባለ:: የደመራ ተቃራኒው ‘ቅነሳና ከፈላ’ ነው::

በነገረ መለኮት ከኛ ጋራ አንድ የሆኑት አኀት አብያተ ክርስቲያናት፤ ከኛ ጋራ በማይካፈሉት በአገራችን በተፈጠረው ታሪካዊ ክስተት ምክንያት፤ በተለየና በደመቀ ሥርዓት በመላ ኢትዮጵያ ይከበራል:: ካህኑ “ደምረነ ምስለ እለ ይድኅኑ” በሚለው በሊጦኑ ቃለ ቡራኬ የመጀመሪያዋን የደመራ መብራት ባርኮ፥ ከደመራው እንጨት ጋራ እንዲደምራት ሕዝቡን በአስተዳደር ለሚመራው ሰው ያቀብለዋል። የሀገሪቱ መሪ ከካህኑ በተቀበለው እሳት የደመራውን እንጨት ይለኩሰዋል:: ከዚያ በኋላ ያገር ሽማግሌና ባካባቢው ያለው ሁሉ በተዋረድ ችቦውን እያቀጣጠለ በደመራው ላይ ይጨምረዋል:: በዚህ ሥርዓት የሚከበረውን የደመራ በዓል በሃይማኖታችን፥ በታሪካችንና በባህላችን አንጸር በመጠኑ እገልጻለሁ::
⇒ በሃይማኖታችን፥
⇒ በታሪካችንና በባሕላችን
ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

ፋሲካ (ትንሣዔ)

ጾሙን ፈጽመን ፋሲካን (ትንሣዔን) ስናከብር ደግሞ “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐጺባ በደመ ክርስቶስ” ማለትም፦ ሰው ይቅርና ምድርም በክርስቶስ ደም በመታጠቧ የፋሲካውን በዓል ታከብራለች” የሚለውን በመዘመር፥ በክርስቶስ ደም በጸዳው ኅሊናችን፥ በቅንነት በጸዳው አዕምሮሯችን በእውነት በተኳለው ዓይነ ሕሊናችን ከሞት በኋላ የሚጠብቀንን ሕይወት አሻግረን መመልከት መቻላችንንና፥ በአራዊት ጠባይ በተመረዙ አረመኔዎች እጅ ለወደቁት፡ ተስፋ ለቆረጡት፡ የሕይወት ብርሃን የሞራል የመንፈስ ልዕልና ትንሣኤ መሆኑን ለምንሰጠው ምስክርነት ምንጭ ነው:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወኩሉ ሰብእ በበ ሥርአቱ” (፩ኛ ቆሮ ፲፭፡፳፫):: እንዳለው አማኝም ይሁን የማያምን (Atheist) ነኝ የሚልም፥ በተወሰነለት ሰከንድ ይሕችን ዓለም በሞት እስኪሰናበታት ድረስ፥ በግሉም ከኅብረተ ሰቡ ጋርም የሚጋራው ትንግርት በሕይወቱ ቢያንስ አንድ ቀን ሳይገጥመው አይቀርም:: በግልና በጋራ የሚደርሱት አዳዲስ ትንግርቶች ጥቅጥቅ ባለ ጫካ በቅለው ተራርቀው በቆሙ ዛፎች ላይ እንደሚጠመጠሙ ሐረጎች፥ በወራት ርቀት ውስጥ ተፈናጥረው በሚከበሩት እንደፋሲካ (ትንሣኤ) በመሳሰሉት ታላላቅ በዓላት ላይ ይጠመጠማሉ::

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

ቤተ ክስቲያናችን በውጭና በውስጥ የገጠማት ፈተና

የዚህች ጦማር ምንጭ በተለያዩ የሕዝብ መወያያ ድኅረ-ገጾች በመታየት ላይ ያለው ምሕረተአብ አሰፋ ፕሮቴስታንታዊ ጂሀድ ብሎ ያቀረበልን ተማኅጽኖ ነው:: ከአዲስ አባባ ፓስተር ዳዊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሰነዘረው ፕሮቴስታንታዊ ጂሀድና ከዋሸንግተን ዲሲ ርዕሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ቤተ መቅደስ ደፍተራ ገለፈት በጠልሰም መልክ ያወጀው ጂሀድ፥ ያንዲት ሳንቲም ሁለት ገጾች መሆናቸው የሚያስገርም ነገር ሆኗል::

ያንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ሆነው የቀረቡትን የፓስተር ዳዊትንና የደፈትራ ገለፈትን የፈተና ምንጮች በመቅድሟ ገልጬ፥ በማስከተል የፓስተር ዳዊትን ጂሀድ ከቃኘሁ በኋላ፥ ደፍተራ ገለፈት በጠልሰም መልክ ያቀረበውን ከፓስተር ዳዊት ጂሀድ ጋር በማነጻጸር አቀርባለሁ:: ከዚያም የከፋ በደል በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የፈጸመውን በደለኛ ለይቶ በማወቅ፥ አንባቢና ታዛቢ በተለይም እምነቱ ይመለከተኛል የሚለው ወገን ያላንዳች አድልዎ በቅዱሳት መጻሕፍት በተቃኘ ሕሊና የራሱን ፍርድ መስጠት ይችል ዘንድ፥ ከዚህ በተታች በዘረዘርኳቸው አንቀጾች ያዘጋጀሁትን ዝርዝር ሐተታ ከመቅድሟ በኋላ አቀርባለሁ::

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

1 6 7 8 9