ወርኃ(ጾመ) ጽጌ(Video)

የ ሆይ እያሉ ወጣቶች የሚጨፍሩትን ከአገርና ከወቅት ጋራ አዋህደው ቀሲስ አስተርአየ በተለመደው ፈሊጣቸው  በከንሳስ መድኃኔ ዓለም ዓውደ ምህረት ላይ ያቀረቡት ትምህርት ቪዲዮ ተቀርጾ ቀርቧል።

ቀሲስ ባቀረቡት ትምህርታቸው እንደገለጹት፦ በአገራችን በኢትዮጵያ አበባየ ሆይ የሚለውን ጭፍራ ሳይጨፍር፤ ባይጨፍርም ሳይሰማ ያደገ የለም። የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ነገረ መለኮቱን በባህላችን በህይወታችን በታሪካችን ማዋሀዳቸውን ከምናይባቸው ክስተቶች አንዱ አበባየ ሆይ እየተባለ በያመቱ በወጣቶች የሚጨፈረው ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችንን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ልዩ የሚያደርጓትም “አበባዬ ሆይ!ለምለም” እና  የመሳሰሉት በየበዓላቱ በወጣቶችና ባዛውንቱ ሁሉም እንደየ እድሜው የሚታዩት  ተሳትፎዎች ናቸው። ወቅቱ የልምላሜ ያበባ ወቅት ነው። ይህ የልጆች አመታዊ ጭፈራ የወቅቱ መቀብያ ነው። ወቅቱን ተንተርሶ በህዝብ የሚታወሰው ወቅት የጽጌ ጾም    ይባላል ።

ጾሙ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከጌታችን ጋራ በተሰደደች ጊዜ የደረሰባቸውን መከራ ስደት የምናስታውስበት ወቅት ነው። ከጽጌ ጋራ ለምን እንደተያያዘ እንዲህ ሲሉ በሰፊው ገልጸውታል።  ጾመ ጽጌ ማለት የአበባ ጾም ማለት ነው።  አበባ ከምድር ማህጸን የሚከሰት የምድር ጌጥ፤ የምድር ውበትና የምድር ፍሬ መገኛ ነው። የዚህ ሁሉ ውበት ስብስብና ድምር  የፍጥረት መደምደሚያ ሰውነታች ነው። የቅድስናችን ውበት ሲበከል ሰውነታችንን ማለትም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ሰውነት ቀድሶ አንጽቶ ለበሰው። የክርስቶስ ሰውነት ከመቤታችን የወሰደው የተወሀደው ነው። በመስቀል ላይ ከክርስቶስ አካል የፈሰሰው ውሀና  ደም ከመሬት የተገኘ የዳንበት ጽጌ ረዳ ነው።

ወቅታዊውን ችግር ለማንጸባረቅም የሚከተለውን ተናግረዋል። “አንተ አፈር ነህ፤ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” ተብለን በልደት ወደዚህ ዓለም የመጣንባትና  ተመልሰን የምንገባባት የመሬታችን የኢትዮጵያ ደም ግባት  የአበባዋና የውበቷ  መፍለቂያ ገባር ወንዞችን የሚሰበስበው ዓባይ ወይም  ጣና ነው። አባይ ከደረቀ የኢትዮጵያ ልምላሜ ይጠወልጋል። አበባነቷም ይረግፋል። የእናት አገራችን አበባነቷ እንዳይረግፍ በሚደረገው መታደግ እንትባበር ዘንድ ፈጣሪ እንዲረዳን እንጸልይ“ ካሉ በኋላ፤ በቤተ ክርስቲያናች ትውፊት የሚቀርበው ትምህርትና ጸሎት ከህዝብና ካገር ነባራዊ ሁኔታ  ተበጥሶ፤ ተቆርጦና በወቅቶች ከሚከሰቱ ነገሮች ሁሉ ተለይቶ የሚቀርብ  አይደለም ብለው፤ ”ደምን በመአዛ መተካት ስህተት ነው” ብለው “በደም ፋንታ መዓዛ መባል አለበት” ተብሎ በስህተት ተነገረ የሚባለውም እንዲታረም እግር መንገዳቸውንም በማሳሰብ፤  በከንሳስ መድኃኔ ዓለም ዓውደ  ምህረት ላይ ያቀረቡትን ዓመታዊ ትምህርት ይጠቅማል ብለን ስለገመትን ቪዲዮውን ከዚህ በታች አቅርበንላችኋል።